የፌዴሬሽን ምክር ቤት

የፌዴሬሽን ምክር ቤት

በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ አሳዛኝና አሳፋሪ ጥቃት ተፈጽሟል ብሏል

ኢዛ (ሐሙስ ጥቅምት ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 5, 2020)፦ ከትናንት በስቲያ ምሽት ላይ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተለያዩ ተቋማት ድርጊቱን በማውገዝ አቋማቸውን እያስታወቁ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ተገቢውን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።

“የአገራችን ልዩ መለያ የኾነው ጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊታችን፤ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ዳር ድንበርንና ሉዓላዊነትን በማስከበር ተልዕኮ ላይ እያለ በደም የሰከሩ፣ ከሃዲና የእናት ጡት ነካሾች አሳቻ ጊዜ ጠብቀው፤ አሳዛኝና አሳፋሪ ጥቃት ፈጽመውበታል” በማለትም በመግለጫው ላይ አስታውቋል።

የመከላከያ ሠራዊት ለረዥም ጊዜያት በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚቃጣን ጥቃት ጋሻና መከታ በመኾን ራሳቸውን መሥዋዕት በማድረግ ሲከላከሉላቸው መቆየታቸውን ያመለከተው ይህ መግለጫ፤ ከዚህም በላይ የተፈጥሮ አደጋ ክስተት ሲከሰት፣ ሲታደጉና በልማት መስኮችም ተሰልፈው በጉልበታቸውና በገንዘባቸው በመርዳት የወገን አለኝታነታቸውን ያስመሰከሩ ጀግና የቁርጥ ቀንና የሕዝብ ልጆች ናቸው ሲልም ገልጿል።

ለእነዚህ ለቁርጥ ቀን ጀግኖቻችን ክብር፣ ሽልማትና ሞገስ ሲገባቸው በሚመኩባቸው ወገኖቻችንና ወንድሞቻችን በሚሉት ከሃዲዎች የተፈጸመውን አስነዋሪ ጥቃት ምክር ቤቱ በጽኑ እንደሚያወግዘውም በመግለጫው ላይ አስታውቋል። ስለኾነም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ከአካባቢያቸው ጀምሮ እስከ አገር ጠንካራና የተቀናጀ ጥንቃቄ በማድረግ በሚያስፈልገው ሁሉ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እንዲቆሙና ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን ያስተላልፋል ብሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ