በወይዘሮ ኬርያ ምትክ አዲስ አፈ ጉባዔ ተመረጠ
አዲሱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ
ምክትል አፈ ጉባዔውም በአዲስ ተተክተዋል
ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 10, 2020)፦ ሕጋዊ በኾነና ሥርዓትን በጠበቀ መንገድ ኃላፊነታቸውን ባለመልቀቃቸው ትችት እየቀረበባቸው ባሉት የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሒም ምትክ አዲስ አፈ ጉባዔ ተመረጠ።
ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን መቀሌ ኾነው በገለጹት የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሒም ምትክ፤ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የመረጣቸው አዲሱ አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ ናቸው። እስካሁን በምክትል አፈ ጉባዔነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ መሐመድ ረሽድ ሐጂ ደግሞ ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው በመልቀቃቸው፤ አዲስ ምክትል አፈ ጉባዔ ተመርጧል።
አቶ ረሽድ ኃላፊነታቸውን በፍቃዳቸው የለቀቁት፤ በዛሬው ዕለት የተመረጡት አዲስ አፈ ጉባዔ ከሶማሌ ክልል በመኾናቸው፤ እራቸውም ከዛው ክልል የተወከሉ በመኾኑ፤ ከአንድ ክልል ሁለቱን ቦታዎች ከመያዝ፤ ለሌላ ዕድል ለመስጠት በማሰብ ነው ተብሏል።
በዚሁ መሠረት ዛሬ ከሰዓት በተካሔደው የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ስብሰባ፤ አቶ መሐመድ ረሽድን ተክተው ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ኾነው ተመርጠዋል። (ኢዛ)



