በተቀዛቀዘ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አሥር በመቶ ጨምሯል
ጫት
አበባ፣ ጫት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው
ኢዛ (ሰኞ ግንቦት ፲ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 18, 2020)፦ የዓለም ኢኮኖሚ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ በተመታበት በዚህ ወቅት፤ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አፈፃፀም ከቀደሙት ወቅቶች የተሻለ በመኾን በዘጠኝ ወራት 2.09 (ሁለት ነጥብ ዜሮ ዘጠኝ) ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተመለከተ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአገሪቱን የ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር የወጪ ንግድ አፈፃፀም አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት፤ በዘጠኝ ወር ውስጥ 2.09 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱንና ይህም በ2011 በጀት ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው ገቢ የአሥር በመቶ ብልጫ ያለው ኾኖ መገኘቱን አስታውቋል።
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ግን 2.7 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት የታቀደ እንደነበር የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
ከእቅዱ አንፃር ከ780 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የተገኘ ቢኾንም፤ በ2012 በጀት ዓመት የተመዘገው የ2.09 ቢሊዮን ዶላር ገቢ፤ ከዚህ ቀደም በተከታታይ ዓመታት በተመሳሳይ ጊዜ ከተገኘው ገቢ አንፃር ትልቅ ለውጥ የታየበት አፈፃፀም እንደኾነ ይታመናል።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዓለም ደረጃ ንግድ የተቀዛቀዘ ቢኾንም፤ የኢትዮጵያ የመጨመሩ ምክንያት ለምን? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፈንቴ፤ “በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በዓለም ደረጃ የንግድ ግንኙነት የተቀዛቀዘ ቢኾንም፤ ኢትዮጵያ እያመረተች ያለችው ለምግብነት የሚውሉ ምርቶች በመኾናቸው፤ ገቢው ሊጨምር ችሏል” ብለዋል።
በዘጠኝ ወር ውስጥ ከእቅድ በላይ ገቢ ያስገኙ ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ አበባ፣ ጫት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ናቸው። አቶ ወንድሙ እንደገለጹት ከኾነ፤ የብዕርና አገዳ እህሎች፣ የተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን፣ ቡና፣ ኤሌክትሮኒክስ እንዲሁም ጨርቃጨርቅና አልባሳት የእቅዱን ከ75 በመቶ በላይ፣ ታንታለም፣ የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ ሥጋ፣ ቅመማ ቅመም፣ ባሕር ዛፍ እና ሻይ ቅጠል የእቅዱን ከ50 እስከ 74 በመቶ ገቢ አስገኝተዋል። የእቅዱን ከ50 በመቶ በታች ዝቅተኛ ገቢ ያስገኙ ምርቶች ደግሞ ወርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እና የቁም እንሰሳት ናቸው። (ኢዛ)



