National Election Board of Ethiopia

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ፓርቲዎቹ ጊዜ ተሠጥቷቸዋል

ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፲፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 24, 2020)፦ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ምርጫ አዋጅ መሠረት እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ማሟላት ያለባቸውን ግዴታ ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ መሠረት፤ ፓርቲዎች ማሟላት ያለባቸውን ሁኔታዎች በሙሉ አሟልተው ምዝገባ እንዲጀምሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አጥብቆ አሳሰበ።

ቦርዱ ዛሬ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳስታወቀው፤ ቦርዱ በደብዳቤና ማሟላት የሚጠበቅባቸውን ዝርዝር ሁኔታዎችን የሚያስረዱ ሰነዶች የደረሳቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. የተጠየቁትና ማሟላት የሚገባቸውን በሙሉ አሟልተው የምዝገባውን ሥርዓት እንዲጀምሩም ማስታወቂያ አውጥቷል።

ቦርዱ ዛሬ የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ለፖለቲካ ድርጅቶች ያስተላለፈው ሙሉ መልእክት ይህ ነው፤ (ኢዛ)

ማስታወቂያ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ምርጫ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በዚሁ አዋጅ መሠረት በቦርዱ አገር አቀፍና የክልል ፓርቲዎች ማሟላት ያለባቸው ግዴታ ለማስፈጸም የወጣው መመሪያ ቁጥር 03/2012 መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ማሟላት የሚገባቸውን ዝርዝር ሁኔታ የሚያስረዱ ሰነዶች ማዘጋጀቱና ለፓርቲዎች እንዲደርሳቸው ማድረጉ ይታወሳል።

እነዚህ ሰነዶች ለእያንዳንዱ ፓርቲ ከተጻፈ ደብዳቤ ጋር በአባሪነት ተያይዘው እንዲደርሳቸው ሲደረግ፤ በደብዳቤው ላይ በግልጽ እንደሰፈረው ሟሟላት የሚገባቸውን ሁኔታዎች ሁሉ እስከ መጋቢት 03 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ አሟልተው እንዲያቀርቡና ምዝገባቸውን እንዲያድሱ በግልጽ በማስታወቅ ጭምር ነበር።

ነገር ግን እስከአሁን ሰነዶቻቸውን ያስገቡ ፓርቲዎች ቁጥር ዝቅተኛ በመኾኑ፤ ፓርቲዎቹ እንዲያሟሉት በዝርዝር የተገለጸላቸውን ሁኔታዎች በተሠጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ አሟልተው እንዲያቀርቡ ቦርዱ ይህንን ማስታወቂያ ማውጣት አስፈላጊ ኾኖ አግኝቶታል።

ስለዚህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤና ሟሟላት የሚጠበቅባቸው ዝርዝር ሁኔታዎችን የሚያስረዱ ሰነዶች የደረሳችሁ የፖለቲካ ፓርቲዊች በሙሉ፤ በደብዳቤ በተገለጸው የጊዜ ገደብ ማለትም መጋቢት 03 ቀን 2012 ከመድረሱ በፊት ሟሟላት የሚገባቸውን በሙሉ አሟልታችሁ የምዝገባውን ሥርዓት እንድትጀምሩ በዚህ ማስታወቂያ ቦርዱ አጥብቆ ያሳስባል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ