ቆምጨጭ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ - ፩
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው የፓርላማ ውሏቸው ማብራሪያ ሲሰጡ (ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም.)
- የግል ዘርፍ ብድር መንበሽበሽ
- የኤርትራ ሠራዊት እና የተያያዙ ጉዳዮች
- እፍርታም የተባሉት የፖለቲካ ድርጅቶች
- የህዳሴ ግድቡ ያልታሰበው የ20 ቢሊዮን ብር ወጪ
ኢዛ (ማክሰኞ መጋቢት ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 23, 2021)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የዛሬው የፓርላማ ውሏቸው ለየት ብሎ የሚታይ ነው ሊባል ይችላል። በዛሬው (ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም.) የፓርላማ ማብራሪያቸው በዋናነት የአሥር ዓመቱን የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ የሚመለከት ቢኾንም፤ ወቅታዊ በኾኑ ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ከሕዝብ ተወካዮች አባላት የቀረቡ ጥያቄዎችን መሠረት ያደረጉ ምላሾችንም ሰጥተዋል።
ከሌላው ጊዜ ለየት ብሎ ረዘም ያለ ጊዜ በወሰደው የዛሬው የፓርላማ ውሎ በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሱ ሲሆን፤ የመንግሥታቸውን አቋም ያንጸባረቁት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነበር። ለአንዳንድ ጥያቄዎችም ቆምጨጭ፣ ቆጣ ብለው ምላሽ የሰጡባቸው ሐሳቦች ነበሩ ማለት ይቻላል።
ከወቅታዊ አገራዊ ኢኮኖሚ አንጻር በአኀዝ ጭምር ተደግፈው ከቀረቡት ማብራሪያዎቻቸው መኻል፤ ኢትዮጵያ የእዳ ጫናዋን እያቃለለች መምጣትዋን እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የተመዘገበው ውጤት ምን ያህል እንደኾነ ከጠቀሷቸው መኻል፤ የአገሪቱ የእዳ ጫና በ2010 ዓ.ም. ከነበረበት 36.6 በመቶ በ2012 ወደ 26.8 በመቶ ዝቅ ብሏል። ይህም አገሪቱ ተጨማሪ ብድር እንዳታገኝ አድርጓት የነበረውን ጫና በመቀነስ፤ ተጨማሪ ብድር እንድታገኝ አስችሏታል።

የግል ዘርፍ ብድር መንበሽበሽ
ኢኮኖሚያዊ ከኾኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከተሰጠባቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ ባንኮች ለግል ዘርፉ እየሰጡ ያሉት ብድር ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱ አንዱ ነው።
በዛሬው አንደበታቸው በአኀዝ እንዳቀረቡት፤ በ2010 ባንኮች ከሰጡት 170 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለግል ዘርፉ የተሰጠው 45 በመቶ ብቻ እንደነበር አስታውሰው፤ ቀሪው 55 በመቶ መንግሥት የወሰደው ነበር ብለዋል። ከአንድ ዓመት በኋላ በ2011 ዓ.ም. የግል ዘርፉን ለማነቃቃት ተብሎ አቅጣጫ በመያዙ፤ ለብድር ከዋለው 236 ቢሊዮን ብር 61 በመቶው ለግሉ ዘርፍ እንዲሰጥና የመንግሥት ድርሻ 39 በመቶ እንዲኾን መደረጉን አስረድተዋል።
ለግል ዘርፉ የሚሰጠው ብድር አሁንም እያደገ በመምጣቱ፤ በ2013 በስምንት ወራት ከተለቀቀው ብድር ውስጥ 74 በመቶው ለግል ዘርፉ የተሰጠ መኾኑን ገልጸው፤ ይህ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንጻር እንደ ስኬት የሚታይ ነው ብለዋል።
በወጪ ንግድም ከለውጡ በኋላ ትልቅ ለውጥ የታየበት ነው ብለዋል። ከገቢ አንጻርም መንግሥት በየዓመቱ 20 እና 30 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ ገቢ እያገኘ መምጣቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ግን በቂ ያለመኾኑንም ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ መነቃቃት እየታየበት መኾኑን ለማስረዳት የሞከሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን የሚታየው የሲሚንቶ እና የብረት እጥረትም ከዚሁ የኢኮኖሚ እድገት እና የቆሙ ግንባታዎች ወደ ሥራ እየገቡ መኾኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የኤርትራ ሠራዊት እና የተያያዙ ጉዳዮች
በዛሬው የፓርላማ ውሎ የብዙዎችን ትኩረት ከሳበው ማብራሪያቸው ውስጥ የኤርትራ ሠራዊትን የሚመለከት ነው። በብዙዎች አመለካከት የኤርትራ ሠራዊት የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ መግባቱን መንግሥት ያመነበት ነው እስከመባል ደርሷል።
በዚህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያቸውን የጀመሩት፤ “ወዳጅም ጠላትም ማወቅ ያለበት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ሕዝብ እና የመከላከያ ሠራዊት ክህደት ተፈጽሞበት፤ በገዛ ወገኖቹ ጥፋት ሲካሔድበት፤ የኤርትራ ሕዝብ እና መንግሥት ወደሱ የሔዱትን ወታደሮች የያዘበት ወደፈለጉበት እንዲሔዱና እንዲደርሱ ድጋፍ ያደረገበትን መንገድ፤ የሁልጊዜ የኢትዮጵያ ባለውለታ ያደርገዋል” በማለት ነበር።
የኤርትራ ሕዝብ እና መንግሥት ስላደረገው ነገር በጣም ነው የምናመሰግነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ የገለጹት ደግሞ፤ ከዚህ በኋላ የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ በትግራይ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ፤ በእኛ ሕዝብ ላይ በማንኛውም መንገድ በጥፋት ደረጃ በሚገለጽ መልኩ የሚያደርጋቸውን ጥፋቶች ግን አንቀበልም ብለዋል።
ይህንን የማንቀበለው የኤርትራ ወታደር ስለኾነ ሳይኾን፤ የኢትዮጵያ ወታደርም ቢኾን ካደረገው በፍጹም አንቀበለውም በማለት ተናግረዋል። ይህንን የማይቀበሉትም በትግራይ የተካሔደው ዘመቻ በግልጽ ከተለዩ ጠላቶቻችን ጋር እንጂ ከሕዝባችን ጋር አይደለም በማለት አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ተደጋጋሚ ምክክር መደረጉንም አስታውሰው፤ በቅርቡም ተጨማሪ ውይይት እንደሚደረግም ገልጸዋል።
በኤርትራ መንግሥት በኩል ግን፤ ድንበሮችን አልፎ ያለባቸውን አካባቢዎች በሚመለከት የሚያነሳው መከራከሪያ ጉዳይ፤ ላለፉት 20 ዓመታት የኢትዮጵያ መከላከያ የነበረበትን በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መኻል ያለውን ምሽግ ለቃችሁ ሔዳችኋል፤ የጁንታው ኃይል ወደ ውጊያው እንድንገባ ሮኬት እየተኮሰ ጋብዞናል ማለታቸውን ጠቅሰዋል።
አሁን ደግሞ እናንተ ይሔን ምሽግ ለቅቃችሁ ወደ መኻል ትግራይ ጠላት ፍለጋ እየሔዳችሁ፤ እዚያ ስለኾነ ስታጠቁት ተገልብጦ ወደ እኛ ሊመጣ ይችላል ማለታቸውን በመጥቀስ፤ ዶ/ር ዐቢይ የኤርትራን መከራከሪያ ነጥብ አመላክተዋል።
ይህንንም ከብሔራዊ ደኅንነት አኳያ የሚመለከቱት እንደኾነም እንደገለጹላቸውና ለዚህም ድንበር አካባቢ ያሉትን ቦታዎች ኤርትራውያን መያዛቸውን ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያ ወታደር ምሽጉን የሚቆጣጠር ከኾነ በማግሥቱ የሚለቁ እንደኾነ እና በተለይም በያዙት መቆየት እንደማይፈልጉም መናገራቸውን ለፓርላማው ገልጸዋል።
የኤርትራ ወታደሮች ዘረፋ ያካሒዳሉ በሚለው ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ቀርቦ እንደነበርም ዶ/ር ዐቢይ አስታውሰው፤ የኤርትራ መንግሥት ድርጊቱን መኮነኑንና በዚህ ድርጊት የኤርትራ ወታደሮ ተሳትፈው ከኾነም እርምጃ ይወሰዳል ማለታቸውን ገልጸዋል።
እፍርታም የተባሉት የፖለቲካ ድርጅቶች
ቆምጨጭ ያለ ምላሽ ከሰጡባቸው እና የመንግሥታቸውን አቋም በግልጽ ካሳዩባቸው ከዛሬው ምላሾቻቸው መካከል፤ ምርጫን በተመለከተ የሰጡት ማብራሪያ ተጠቃሽ ነው። ምርጫው ምንም ይሁን ምን ይካሔዳል ብለዋል። ምርጫው ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾነ መንግሥታቸው በብርቱ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈ በዚህ ምርጫ አንሳተፍም ስሳሉት ፓርቲዎች ግን በብርቱ ኮንነዋል።
እንዲያውም በምርጫው አንሳተፍም ያሉትን ፓርቲዎች፤ “በሕወሓት ዘመን የምርጫ አጃቢዎችና አሯሯጮች ነበሩ” እስከ ማለት የደረሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “እፍርታሞች” ብለዋቸዋል።
በሕወሓት ጊዜ ከተደረገው ምርጫ የተሻለ ምርጫ በሚካሔድበት በዚህ ምርጫ እንዲሳተፉም ያሉትን ፓርቲዎች፤ እራሳቸው ጭምር በግል ያነጋገሯቸው መኾኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮ ምርጫ ላለመሳተፍ እያሳወቁ የቆዩት ኦፌኮ እና ኦነግ በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆን፤ እንደእፍርታም የተቆጠሩት ፓርቲዎች እነዚሁ ፓርቲዎች እንደኾኑ ይታመናል።
የህዳሴ ግድቡ ያልታሰበው የ20 ቢሊዮን ብር ወጪ
በዛሬው የፓርላማ ውሎ እንደ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነገሩን መረጃዎች መኻል፤ ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የግድቡ ዋነኛ ኮንስትራክተር የኾነው የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ከዚህ ቀደም ከነበረው የአሠራር ብልሹነት አንጻር፤ አንድ ቢሊዮን ዶላር የካሣ ክፍያ መጠየቁን ነው።
ይህ ሳሊኒ ሊከፈለኝ ይገባል ብሎ የጠየቀው አንድ ቢሊዮን ዶላር ላይ ብዙ ድርድር ተደርጎ ከብዙ ልፋት በኋላ ወደ 450 ሚሊዮን ዩሮ ለመክፈል ተስማምተው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የተፈጠረው ሙግት ባለፈው ሳምንት መቋጨቱን አሳውቀዋል። ይህ አሁን ባለው ምንዛሪ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ መኾኑንም አመልክተዋል።
የህዳሴ ግድብ ላይ የነበረው የፕሮጀክት የአፈጻጸም ችግር እንዲህ ያለ ያልተገባ ወጪ ስለመውጣቱ የሚያሳይ ነው። ይህም ቢኾን ግን ግድቡ ይጠናቀቃል ያሉት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ ሁለተኛው የግድቡ የውኃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ የሚካሔድ ስለመኾኑም አስታውቀዋል። (ኢዛ)



