የቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ንዋይ ገብረአብ አረፉ
የቀድሞዎቹን ጠቅላይ ሚኒስትሮች፤ አቶ መለስ ዜናዊንና አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በኢኮኖሚ አማካሪነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ንዋይ ገብረአብ
ለሃያ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው
ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፲፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 24, 2020)፦ የቀድሞዎቹን ጠቅላይ ሚኒስትሮች በኢኮኖሚ አማካሪነት ሲያገለግሉ የቆዩትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን በቦርድ ሊቀመንበርነት በመምራት የሚታወቁት አቶ ንዋይ ገብረአብ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተና ሚና የነበራቸው አቶ ንዋይ የቀድሞዎቹን ጠቅላይ ሚኒስትሮች፤ አቶ መለስ ዜናዊንና አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በኢኮኖሚ አማካሪነት አገልግለዋል።
ከዚህም ሌላ ለ25 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን በቦርድ አባልነትና ሰብሳቢነት ያገለገሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ልማትና ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር በመኾን ከማገልገላቸውም በላይ፤ በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ሲሠሩ ቆይተዋል።
ከ25 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀረጻና ማስፈጸም ላይ የጎላ ሚና የነበራቸው አቶ ንዋይ፤ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና ቀረጻ ላይም ጉልህ ድርሻ የነበራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያ እንደነበሩ ይታወቃል።
አቶ ንዋይ ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት የተበደረቻቸውን እዳዎች ለማሰረዝ የዛሬ 27 ዓመት የተቋቋመውን ቡድን ሲመሩ የቆዩ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ እዳዎችን ማሰረዝ መቻላቸው ይነገራል። አቶ ንዋይ በጡረታ የተሰናበቱት የዛሬ 3 ዓመት ነበር።
አቶ ንዋይ ባጋጠማቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ፤ ዛሬ ጠዋት የካቲት 16 ቀን 2012 ዓም. ማረፋቸውን ለማወቅ ተችሏል። (ኢዛ)



