Logo

አምባሳደር ጀፍሪ ፊልትማን

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ጀፍሪ ፊልትማን

በህዳሴው ግድብ ላይ የመጀመሪያውን ውይይት እያደረጉ ነው

ኢዛ (ሰኞ ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 10, 2021)፦ አነጋጋሪው የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ጀፍሪ ፊልትማን አዲስ አበባ ገብተዋል። በህዳሴው ግድብ ላይ የመጀመሪያውን ውይይት እያደረጉ ነው።

አምባሳደሩ የመጀመሪያ ውይይታቸውንም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂንየር ስለሺ በቀለ ጋር በመገናኘት በግድቡና በሦስትዮሽ ድርድር ዙሪያ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

የአሜሪካው ልዑክ በተለይ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተንሸዋረረ አመለካከት ያላቸው ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ተጨማሪ ውይይቶችን ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የልዩ መልእክተኛው ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በተለያዩ ወገኖች የተለያየ አስተያየት የሚሰጥበት ቢሆንም፤ በምሥራቅ አፍሪካ እያደረጉ ካሉት ጉብኝት በቀንዱ የሚገኙ አገራት ያለውን የፖለቲካ፣ የጸጥታና ሰብአዊ ችግሮች በዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲፈቱ ለማስቻል እንደኾነ ተነግሯል።

ከዚህም ሌላ አሜሪካ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን የፖሊሲ ትብብር ማጠናከር እሳቤ ያለው ጉብኝት እንደኾነም ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ከመግባታቸው ቀደም ብሎ ግብጽ፣ ሱዳን እና ኤርትራን መጎብኘታቸው ይታወሳል። (ኢዛ)

© ፳፻ - ፳፻፲፬ ዓ.ም. ኢትዮጵያ ዛሬ፣ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ነው። Copyright © 2007 - 2022 Ethiopia Zare. All Rights Reserved.