Svensk grammatik på amhariska för nybörjare

“የስዊድንኛ ሰዋስው በአማርኛ ለጀማሪዎች (Svensk grammatik på amhariska för nybörjare)” በሰለሞን ሐለፎም

ኢዛ (ሐሙስ ግንቦት ፰ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም. May 16, 2019):- የስዊድንኛ ሰዋስው በአማርኛ ለጀማሪዎች (Svensk grammatik på amhariska för nybörjare) በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን መጽሐፍ ደራሲ ሰለሞን ሐለፎም ሜይ 5 ቀን 2019 እ.ኤ.አ. (ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም) በስቶክሆልም አስመረቀ።

ደራሲ ሰለሞን ሐለፎም “የስዊድንኛ ሰዋስው በአማርኛ ለጀማሪዎች (Svensk grammatik på amhariska för nybörjare)” የተሰኘው መጽሐፍ ምረቃ ሥነሥርዓት ላይ ሲፈርም

በመጽሐፉ ምረቃ ሥነሥርዓት ላይ የደራሲው ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፣ ደራሲ ሰለሞን ስለመጽሐፉ ይዘትና አዘገጃጀት ማብራሪያ ሰጥቷል። እንዲሁም ከታዳሚው በመጽሐፉ ዙርያ ለተነሱ ጥያቄዎችም መልስ ሰጥቷል። ከጥያቄዎቹ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ መጽሐፉ ቀጣይ ሥራዎች ይኖሩት እንደሆን፤ መጽሐፉን ለማዘጋጀት ያነሳሳው ምክንያት ምን እንደሆነ፤ ሥራው ምን ያህል ጊዜ እንደፈጀበት፤ መጽሐፉ ለአብዛኛው የስዊድን ቋንቋ ጀማሪዎች እንዲዳረስ የታሰበ ምን ዐይነት ዝግጀት እንዳለ፤ እንዲሁም ለዚህ መጽሐፍ ሕትመት የሚያግዝ ድርጀት አግኝቶ እንደሆነ የሚሉ ነበሩ።

ደራሲው ጥያቄዎቹን በቅደም ተከተል ሲመልስ፤ ቀጣይ ሥራ ለማዘጋጀት በተጠቃሚው ፍላጎት አኳያ የሚለካ መሆኑን ገልጾ፣ አብዛኛዎች የዚህ መጽሐፍ ተጠቃሚ ከሆኑና ቀጣይ ሥራ እንደሚያስፈልግ ጠቋሚ መረጃ ከተገኘ በኔ በኩል ዝግጅቱን ለመቀጠል ፈቃደኛ ነኝ ብሏል። መጽሐፉን ለማዘጋጀት ያነሳሳኝ ደግሞ አብዛኛው ቋንቋ ተማሪ ያለበትን ችግር በመረዳት፤ ለዚህ ችግር አቋራጭ መፍትሔ ለመፈለግ እንደሆነ ገልጾ፤ አንድ ጫካ ውስጥ ሆኖ መንገድ የጠፋው ሰው መሪ አግኝቶ ወዴት እንደሚሄድ የማሳየት ያሕል ቋንቋውን ለመረዳት እንደሚያስችል በመረዳት ነው ብሏል።

መጽሐፉን ለማዘጋጀት ስለፈጀበት ጊዜ ሲመልስ፤ ምንም እንኳን መጽሐፉ አነስተኛ ገጽ ኖሮት ቢታይም ሌሎች ትላልቅ መጻሕፍት ስጽፍ ከወሰደብኝ ጊዜ በላይ ፈጅቷል። ይህም የሆነበት ምክንያት ቋንቋውን ለማወቅ አስፈላጊ የሆኑትን የሰዋስው ክፍሎች ለቅሞ ማውጣት እጅግ አስቸጋሪና ብዙ ማሰብና ደጋግሞ መሥራት የሚያስፈልግ በመሆኑ ሲሆን፤ መጽሐፉ ግን አንድ ቤት ለማቆም የአሸዋና የሲሚንቶን ያሕል ለቋንቋ እውቀት አቅም እንዳለው አስረድቷል።

መጽሐፉን ለተጠቃሚው ለማድረስ እንዴት ይቻላል ለተባለው ሲመልስ ደግሞ፤ እጅግ ብዙ መንገዶች መኖራቸውን ገልጾ፣ በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል ጎልማሳ ተማሪዎች በሚገኙባቸው መማሪያ ቦታዎች (Sfi skolor)፣ በስዊድን ባሉ ቤተ መጻሕፍት ቤቶች (bibliotek) በመደበኛ ት/ ቤቶች (grundskolor)፣ እና እንደ ሲዳና ቀይ መስቀል አቀፍ ተቋማት በመነጋገር ሊወስዷቸው እንደሚችሉ የታመነበት እንደሆነና ከነዚህ ውስጥ መልስ የሰጡም እንዳሉ አሳውቋል። ለዚህ መጽሐፍም ሆነ ከዚህ በፊት ላሳተማቸው መጻሕፍት ከማንም ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ምንም ዐይነት የማሳተሚያም ሆነ ሌላ እርዳታ እንዳላገኘም አሳውቋል።

በተጨማሪ ስለመጽሐፉ ይዘት በሰጠው ማብራሪያ፤ ሰዋስው የቋንቋን ልዩ ልዩ ክፍሎች አደረጃጀት የያዘ በመኾኑ ወርደ ሰፊ ስለሆነ ሁሉን ነገር ዳስሶ ማቅረብ አስቸጋሪ ቢሆንም፤ በንግግርም ሆነ በጽሑፍ መስተጋብር ወቅት ጀማሪዎች ትኩረት ሰጥተው ሊያውቋቸው የሚገባቸውን ነገሮች በመምረጥ ለማቅረብ እንደቻለና ለዚሁም በምሳሌ የተደገፈ ማብራሪያ መስጠቱን አሳውቋል። መጽሐፉ የያዛቸውን ዋና ዋና ትምህርታዊ ይዘትም ሲገልጽ፤ የንግግር ድምጾች አነባበብና አሰዳደር (አሰካክ)፣ የቃላት ክፍሎች ባሕርያት አረባብና አመሠራረት፣ የሐረግ ዐይነቶችና አወቃቀር፣ የዐረፍተ ነገር መሠረታዊ ክፍሎችና አወቃቀር ያካተተ ሲሆን፣ በተጨማሪም ለናሙና የቀረቡ አባባሎችና ምኅጻሮችን እንደያዘ አስረድቷል።

ደራሲ ሰለሞን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ስነጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ አማርኛን በማስተማር ዘዴ የማስተርስ ዲግሪ ያለው ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ መለስተኛና ከፍተኛ ት/ ቤቶች ለብዙ ዓመታት በአማርኛ መምህርነት አገልግሏል፡፡ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ደግሞ የቋንቋ ማስተማር ዘዴና ሥነ ልሳን ኮርሶች በመሥጠት ለስድስት ዓመታት ያህል ሲሠራ ቆይቷል።

እዚህ ስዊድን ከመጣ በኋላም በስቶኮልም ዩኒቨርስቲ በዝቅተኛ ክፍል ደረጃ መምህርነት በዲግሪ ተመርቆ፤ በአሁኑ ጊዜ ስዊድን ውስጥ ለተወለዱ ልጆች አማርኛ ቋንቋ በማስተማር ላይ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ ልጆቹ የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባህል እንዲያውቁ፤ አዲስ የመጡ ወጣቶች ደግሞ ቋንቋ ከተማሩ በኋላ ወደ መደበኛ ክፍል ከመመደባቸው በፊት በመሰናዶ ክፍል ላይ እያሉ መደበኞቹን መምህራን በማገዝ እንደሚሠራ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ገልጾአል።

“ኦኒ ኒስካነን ከሮሱንዳ እስከ ጃንሆይ ሜዳ” በሰለሞን ሐለፎም

ደራሲው ከአሁን በፊት ያሳተማቸው መጻሕፍት፤

1. “የድርሰት አጻጻፍ”፣ 1997 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣

2. “የአማርኛ መማርያ ለሁለተኛ ደረጃ”፣ 2012 (እ.ኤ.አ) በስቶኮልም፣

3. “እምባባሽና ሌሎችም ወጎች”፣ 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሲሆኑ፤ ከዚህ በተጨማሪ የስመ ጥሮቹ ኢትዮጵያውያን የረጅም ርቀት ሯጮች የአበበ ቢቂላ፣ የማሞ ወልዴ፣ የዋሚ ቢራቱ እና የሌሎችም አሠልጣኝ የነበረውን ስዊድናዊ የ"ኦኒ ኒስካነን​" የሕይወት ታሪክ፤ “ኦኒ ኒስካነን ከሮሱንዳ እስከ ጃንሆይ ሜዳ” በሚል ርዕስ ባለፈው ዓመት መጽሐፍ አሰናድቷል፡፡ ይህ መጽሐፍ በስቶክሆልም እና በአዲስ አበባ ታትሞ በአሁኑ ጊዜ በመነበብ ላይ ይገኛል፡፡

ደራሲ ሰለሞን ይህ አሁን ያስመረቀው መጽሐፍ አምስተኛ መጽሐፉ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ካርል ጉስታፍ ቩን ሩሰን ስለተባለው ስዊድናዊ አብራሪ የልጁ ሚስት የሆነችው ሄሊ ቩን ሩሰን “Dödsorsak Ogaden” በሚል ርዕስ በስዊድንኛ ቋንቋ ጽፋ ያሳተመችውን የአብራሪውን የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ወደ አማርኛ በመመለስ የትርጉም ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጾልናል።

ካርል ጉስታፍ ቩን ሩሰን በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ በርከት ያሉ ግልጋሎቶችን ያበረከተ ስዊድናዊ የነበረ ሲሆን፤ በተለይም ድርቅ ባጠቃቸው ቦታዎች ምግብ የጫነ አውሮፕላን በማብረር በምግብ እጦት ከሞት አፋፍ ላይ የደረሱ ኢትዮጵያውያንን በመርዳት የብዙዎችን ሕይወት እንደታደገ ታሪኩ ያስረዳል። ካርል ጉስታፍ በዚሁ ተግባር ላይ እንዳለ በኢትዮጵያ ምድር ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፤ ሥርዓተ ቀብሩ የተፈጸመውም በኢትዮጵያ ምድር ነበር።

ደራሲ ሰለሞን ከድርሰት ሥራውና መደበኛ ከሆነው የቋንቋ አስተማሪነቱ በተጨማሪ “ብሩህ ተስፋ” የተባለ ማኅበር ከጓደኞቹ ጋር በመመሥረትና የማኅበሩ ሰብሳቢ በመሆን አዲስ መጥ የሆኑ ወጣቶችን የስዊድን ቋንቋ በማስተማር፣ በተለያዩ ጉዳዮች ለኢትዮጵያውያኑ የምክር አገልግሎት እና ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት፣ እንዲሁም ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች አሠራር ጋር በማስተዋወቅ ያገለግላል። ማኅበሩ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥ በበጎፍቃድ የተነሳሱ ሰዎች የሚሳረፉበት ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያንን በአባልነት መዝግቦ ያስተናግዳል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ